በሆሳዕና ከተማ ፋይናንስ ጽ/ቤት የመንግስት ውስን ሀብት በተገቢው በመጠቀምና በማስተዳደር የጀመረውን አበረታች እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል ከንቲባ ሳሙኤል ሽጉጤ አሳሰቡ ።

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የሆሳዕና ከተማ በራሱ ገቢ የሚተዳደር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተሰበሰበውን ገቢ በአግባቡ በቁጠባ መጠቀምና ማስተዳደር እንደሚገባም አሳስበዋል ።

የከተማው ፋይናንስ ጽ/ቤት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ሀብትን በቁጠባ በመጠቀምና በራስ ገቢ ማስተዳደር በመቻሉ በክልል ፣በዞን እና በከተማው ፐ/ሰ/የሰው ሀብት ልማት ጽ/ቤት የዋንጫና የምስክር ወረቀት ተሸላሚ መሆኑን ገልፀው ለተገኘው ውጤት ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል ።

አክለውም በከተማችን በተያዘው የበጀት ዓመት ለመሰብሰብ የታቀደው 2.7 ቢሊየን ብር አሟጦ በመሰብሰብ እና ሀብት በቁጠባ በመጠቀም በመንግሥት የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ፣የአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት እና ሌሎች ኢንሼቲቮች በውጤታማነት ለማሳካት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል ።

የሆሳዕና ከተማ ፋይናንስ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ገነት ሰለሞን በበኩላቸው በከተማው የሚሰበሰበ ውስን ሀብት በቁጠባ በመምራት የተሻለ አፈፃፀም እንዲመጣ ጥረት መደረጉን ገልፀዋል ።

አክለውም ጽ/ቤቱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ለበርካታ ዓመታት ሳይከፈል የተወዘፈ 260 ሚሊየን ብር የመንግስት የጡረታ ዕዳ ለማህበራዊ ዋስትና በመክፈል እና ከተማችንን ስማርት ሲቲ ከማድረግ ጋር ተያይዞ በርካታ የግዥ ሥራዎች ማለትም ለኮሪደር ልማት፣ለካልቨርት ሥራ፣ለህዝብ ፋርማሲ ፣የውስጥ ለውስጥ አስፋልት ግንባታ 251,701,093 ብር ወጪ በማድረግ አበረታች እንቅስቃሴ ማድረግ መቻሉን ወ/ሮ ገነት ገልፀዋል ።

ጽ/ቤቱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በተግባር አፈፃፀም የላቀ ውጤት በማስመዝገብ የተገኘው ውጤት ለመድገም ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል ።

የሆሳዕና ከተማ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፋንታሁን ሊረንሶ ፣የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አድነው ባፋ በየበኩላቸው ከቤቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት የሆሳዕና ከተማ ከትላልቅ ከተሞች ተርታ ለማሰለፍ ከብልሹ አሰራር የፀዳ የገቢ ዕቅድ ለማሳካት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ።

በመጨረሻም የጽ/ቤቱ ተግባር እንዲሳካ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አመራሮች እና ባለሙያዎች ዕውቅና በመስጠት የምክክር ጉባኤው ተጠናቋል ።

በነስሩ ባደዢ

 

Share this Post