በፌዴራል የገቢዎች ሚኒስቴር ሀዋሳ ቅርጫፍ ጽ/ቤት በገቢ ግብር አዋጅ 979/2008 ለማሻሻል በወጣው አዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 1395/2017 በተካተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ለዞን፣ለከተማ አስተዳዳሮችና ለወረዳ ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥተዋል ።

በፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የታክስ ከፋዮች ትምህርትና መረጃ አቅርቦት ቡድን አስተባባሪ ወይዘሮ አለምፀሓይ ጭሻ በስልጠናው ወቅት የአዋጁን ማሻሻል አስመልክተው በሰጡት ገለፃ የገቢ ግብር አዋጅ 979/2008 ለማሻሻል የወጣው አዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 1395/2017 ለንግዱ ማህበረሰብ የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል ።

አዲሱ አዋጅ የግብር ስርዓት ላይ የሚታዩ የፍትሃዊነት ችግሮችን በመፍታት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህበረተሰብ ክፍሎች የሚያርፍበትን የግብር ጫና በመቀነስና ሌሎች የግብር መስፈርትን በማስፋት የገቢ አቅም ከፍ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተገልጾአል ።

ይህ አዲሱ የገቢ የግብር አዋጅ የአገሪቱን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበርና ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋ ቢከሰት ቶሎ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ሲሆን ግልጽነት የጎደሉ አንቀጾችን በማረም ለአሰራር አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ተመልክቷል ።

የሀዲያ ዞን ገቢዎች መምሪያ የደንበኞች አገልግሎት የታክስ አወሳሰንና አሰባሰብ ደይሬክቶሬት አስተባባሪ ወይዘሮ ፀጋነሽ ዳንኤል በበኩላቸው በሰጡት አስታያየት አዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ 1395/2017 ከዚህ ቀደም የነበረውን የገቢ ግብር አሰባሰብ ክፍተት በመሙላት የዞናችንን የገቢ መጠን ከፍ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል ።

አዲሱ የገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጅ ለአሰራር አመቺና ግልጽ በሆነ መልኩ የቀረበ በመሆኑ ለግብር ከፋዩም ያለው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑንም አክለው አንስተዋል ።

በዕለቱ ከሰልጣኞች ከስልጠና ይዘት ጋር በተያያዘ የተላያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሳ ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከመድረክ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷ የዕለቱ የስልጠና መድረክ ተጠናቋል ።

በጌታቸው ደስታ

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት መስከረም 26/2018 ዓ.ም

Share this Post